በመጪው ገና በዓል የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዳይኖር ዝግጅት ተደርጓል፡-

የኢት/ያ ኤሌክትሪክ ኣገልግሎት ታህሳስ 26፣2011

በመጪው ገና በዓል የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ እንዳይኖር በቂ ዝግጅት ማድረጉን  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የሀይል መቆራረጥና መዋዠቅ ይታይባቸዋል በተባሉ ቦታዎች የተለያዩ የመልሶ ግንባታ፣ አቅም የማሳደግ፣ የጭነት ማመጣጠንና የቅድመ መከላከል ጥገና ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዮ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ በኤሌክትሪክ ኔትዎርኩ ላይ ከፍተኛ የኃይል መጨናነቅ ሊከሰት ስለሚችል ከምግብ ፋብሪካዎች ውጪ የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ኃይል ቀንሰው እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም መሰረት ኢንዱስትሪዎቹ ከመጪው ታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡00 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡00 ድረስ ኃይል ቀንሰው እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አስቀድሞ በማዘጋጀት የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይ ከምሽቱ 3፡00 እስከ ሌሊቱ 12፡00 ባለው ጊዜ ቢጠቀም ከቀን በተሻለ ኃይል ማግኘት ይችላል፤ የሚፈጠረውንም የኃይል መጨናነቅ ይቀንሳል ብለዋል፡፡

ደንበኞች ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ ማንኛውም ዓይነት መረጃ ሲፈልጉ ወዲያውኑ በአካል ወደ አቅርቢያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በመሄድና በአማራጭነት በአዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞች በነፃ የጥሪ ማዕከል 905 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ 

ኤሌክትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ ከሥራ ሰዓት ውጪ ጥገና ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ ባለሞያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

የቅድመ ክፍያ የቆጣሪ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ካርድ መሙላት ከፈለጉ በበዓሉ ዋዜማ እስከ ምሽቱ 1፡00 ድረስ አገልግሎቱን በሚሰጡ ሁሉም ማዕከሎች ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *