“የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ ይሆናል፡፡”- አይ ኤም ኤፍ፡፡

ይህ ከባዱ ዉድቀት በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ ተብሏል፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ተነበየ። የአይ ኤም ኤፍ ትንበያ የኢትዮጵያ መንግሥት ከገለጸው የ6.1 በመቶ አጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ የወረደ ነው።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች የ2020 ዓመታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ይፋ አድርጓል። በዚህም መሠረት ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሦስት በመቶ እንደሚሆን ገልጿል።
በቀጣዩ ዓመትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጉዳት እንደማይወጣ የገለፀው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2021 የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕደገት 3.1 በመቶ እንደሚሆን ከወዲሁ ገምቷል። ለዚህም በምክንያትነት የገለጸው የሚሰጣት የውጭ የገንዘብ አቅርቦትና ብድር በከፍተኛ የሚያሽቆለቁል በመሆኑ ነው።
እንደ ተቋሙ ትንበያ በ2021 ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች 290 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ፋይናንስ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል አስታውቋል። በተጨማሪም አገሮቹ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንደሚመቱ የገለጸ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ እንደምትሆን አመላክቷል።
አይ ኤም ኤፍ ባወጣው የኢኮኖሚ ሁኔታ ሪፖርት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ ይሆናል ቢልም የብልፅግና እድር ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ በፊት ለህገወጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበር ፊት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ መጠነኛ መቀነስ ቢታይም የ6.1 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ተናግረዋል።
በ2012 ዓ.ም. የዘጠኝ በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖማ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ 6.1 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን የፕላን ኮሚሽን መረጃዎች ማመላከቱን በመግለፅ ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር የ2.9 በመቶ ቅናሽ ቢታይበትም፣ ዕድገቱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከገጠመው የኢኮኖማ ፈተና አንፃር ሲመዘን ትልቅ ዕድገት ነዉ ሲሉ ገልፀዉ ነበር፡፡


0